የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 3/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) የአዲስ አበባ ከተማ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከከተማው ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ጋር በመተባበር የፀረ-ሙስና እርምጃ ተግባራዊ ለማድረግ ባለመው ሀገር አቀፍ ረቂቅ ፓሊሲ ላይ ከወጣቶች ጋር ወይይት አድርጓል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው የሥነምግባርና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፓሊሲ በመልካም ስብዕና የተገነቡ፣ ለሙስና የማይበገሩ ዜጎችን ለማፍራት እና በሙስና የተመዘበረ ሀብት የማስመለስና የማስተዳደር አቅምን በመፍጠር በሙስና ትግሉ ላይ ህዝቡን ባለቤት ለማድረግ እንደ ፍኖተ ካርታ የሚያገለግል መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ ትኩርት አድርጎ የተቀረፀ ረቂቅ ፓሊሲ ላይ ከወጣቶች ጋር መወያየት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፥ ወጣቱ የሀገር ተረካቢና የነገዋን ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም ፓሊሲው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ እና መሠረታዊ የሆነ የሥነምግባር ችግሮች ለመቅረፍ ቁልፍ ድርሻ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ በበኩላቸው ሀገር አቀፍ የሙስና መከላከያ ፓሊሲ በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልፀው፥ የወጣቶች ተሳትፎ አሁን ካለበት ደረጃ እየተሻሻለ መሄዱ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ወጣቶች በሙስና መከላከል ላይ የተደራጀ ትግል በማድረግ በየተቋማት የሚስተዋሉ የሙስና ወንጀሎችን መከላከል ይገባል ሲሉ የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር አሰግደው ኃ/ጊዮርጊስ መናገራቸውን ከኮሚሽኑ የፌስቡክ ገፅ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አሰፋ ቶላ በበኩላቸው የሥነምግባር ጉድለት መነሻው የአስተሳሰብ ችግር መሆኑን ጠቁመው፥ እንደ ወጣት ኃላፊነት የሚሰማው፣ ግብረ ገብነት ያለው በመሆን የፀረ-ሙስናን ትግል ለመቅረፍ ያለመ ፓሊሲ ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መደረጉን ገልፀዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች በሌብነት ውስጥ የተሳተፉና የተገኙ ሰዎች ላይ እየተወሰዱ የሚገኙ እርምጃዎች አስተማሪ መሆን ይገባል ያሉ ሲሆን፥ ሙስናን ለመከላከል እኛ ወጣቶች የራሳችንን ሀላፊነት መወጣት አለብን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
+ There are no comments
Add yours