በኢፌዴሪ የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 8/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) የአብክመ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሀገራዊ የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ከክልል ቢሮዎችና ከልማት ድርጅቶች ከመጡ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተሮችና ኦዲተሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ ፋሲል አለኽኝ የረቂቅ ፖሊሲውን ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን፥ በመድረኩም የረቂቅ ፖሊሲው መነሻ ሀሳቦች፣ አስፈላጊነት፣ መርሆዎች፣ የፖሊሲው ዋና ዋና ጉዳዮች እና አቅጣጫዎች፣ የፖሊሲው ቁልፍ የውጤት መስኮች፣ ፖሊሲዉን የማውጣት ስልጣንና ኃላፊነት እንዲሁም የፖሊሲው የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችን በዝርዝር ማየት ተችሏል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ማሩ ቸኮል በመድረኩ ተገኝተው እንደገለፁት የፖሊሲው መውጣት ለተቋማችን ነፃና ገለልተኛ ሁነን ለመስራት፣ የተቋማችን ማነቆ የሆኑ አሰራሮች እንዲፈቱ፣ የዘመኑ የአደረጃጀትና የአሰራር መዋቀሮችን ለመስራት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ውይይት ለፖሊሲው ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማሰባሰብ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው ተቋሙ ፖሊሲ እንዲኖረው መደረጉ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው፥ መካተትና በትኩረት ቢታዩ ያሏቸውን ሀሳቦች ማንሳት መቻላቸውን ከኮሚሽኑ የፌስቡክ ገፅ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

You May Also Like

More From Author

+ There are no comments

Add yours