የጥቅም ግጭት ምንነትና ጉዳቱን ያውቃሉ?

በሰዎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በፖለቲካዊ መስተጋብራቸው ውስጥ የጥቅም ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ ሰዎች መንግስታዊ በሆኑ ተቋማት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በግል ዘርፉ ተሰማርተው ይሰራሉ፥ ተቋማት የራሳቸዉ ህግ ወይም መተዳደሪያ ደንብ ይኖራቸዋል፡፡

በተቋማት ማቋቋሚያ ህጎች ውስጥ የሰራተኞችን እና የአሰሪዎቻቸውን ስልጣን እና ተግባር ይወስናሉ፡፡ ነገር ግን ተቋማት ዝርዝር በሆኑ መመሪያዎችና ደንቦቻቸው ውስጥ የሰራተኞችንና ኃላፊዎችን መብትና ግዴታዎችን፣ የተፈቀዱና የተከለከሉ ተግባራትን ያስቀምጣሉ፡፡ መሠረታዊ ዓላማው ተጠያቂነትና ኃላፊነትን ለማስፈን ነው፡፡

የጥቅም ግጭት ኃላፊነትን ሊያስከትል የሚችል አንዱ መሰረታዊ ፍሬ ጉዳይ ነው፡፡ በተቋምና በሠራተኛዉ እንዲሁም በተቋምና በኃላፊዉ መካከል የጥቅም ግጭት ቢፈጠሩ በህግ አግባብና የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡

የጥቅም ግጭት ጽንሰ ሀሳብ፡- ጥቅም ለሚለዉ ቃል ወጥ የሆነ ትርጉም ማስቀመጥ የሚያስቸግር ነው፡፡ በተለያዩ ህጎች ውስጥ ጥቅም የተለያየ ትርጉም ተቀምጦለታል፡፡

የጥቅም ግጭት ማለት አንድ የመንግስት ሰራተኛ ወይም ኃላፊ በሥራ ተግባር እና ኃላፊነቱ ዉስጥ ከህዝብ ወይም ከመንግስት፣ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግሉንና የቤተሰቡን እንዲሁም የራሱን ቡድን ጥቅም ማስቀደም ማለት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር የመንግስት ሰራተኛዉ ወይም ኃላፊዉ በሥራ ኃላፊነትና ዉሳኔ ሂደት ውስጥ ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም ሲያገኝ፥ በዚህ ምክንያት የስራ ኃላፊነቱን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሲመራ የጥቅም ግጭት ተከሰተ ይባላል፡፡

የጥቅም ግጭት ከወንጀል ተግባር ጋር ተያይዞ የሚታይበት የህግ አግባብ አለው፡፡ በአንዳንድ ህጎች የጥቅም ግጭትን ከገንዘብ ጥቅምና መብት ከማግኘት እንዲሁም መሻሻልን እንደ ጥቅም የተወሰደበት አግባብ አለ፡፡

የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 – ጥቅም ማለት በገንዘብ ወይም በማናቸውም ዋጋ ባለው መያዣ ወይም በሌላ ንብረት ወይም በንብረት ላይ ያለን ጥቅም (መብት)፣ ማንኛውንም ሹመት፣ ቅጥር ወይም ውል፣ ብድርን፣ ግዴታን ወይም ማናቸውንም ዕዳ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈልን፣ ማስቀረትን፣ ማወራረድን ወይም ከእነዚህ ነገሮች ነፃ ማድረግን፣ ከተመሰረተ ወይም ካልተመሰረተ የአስተዳደር፣ የፍትሃብሔር ወይም የወንጀል ክስ ወይም ካስከተለው ወይም ከሚያስከትለው ማናቸውም ቅጣት ወይም የችሎታ ማጣት በማዳን ወይም ይህን በመሰለ ዘዴ የሚደረግን አገልግሎት ወይም ውለታ፣ ማናቸውንም መብት ወይም ግዴታ መፈጸምን ወይም ከመፈጸም መታቀብን፣ በገንዘብ የማይተመን ማናቸውንም ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት በተመለከተ የሚገኝ እንደ ጥቅም ተደርጎ ተወስዷል፡፡

በዚህ መልኩ የተገኘ ጥቅም ከጥቅም ግጭትነቱ ባለፈ የወንጀል ኃላፊነትን ጭምር የሚያስከትል መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ የጥቅም ግጭት እንደየተቋማቱ ህጎች የሚለያይ ሲሆን፥ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ በአንድ ተቋም ሥር የሚተዳደሩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በመጣስ የሚያስተዳድሯቸውን ተቋም ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ወይም ሊያጋጭ የሚችል ተግባር ፈጽመዉ ሲገኙ የጥቅም ግጭት የሚፈጠር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድሩ ተቋማት የሰራተኞችን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ፈፅመዉ ሲገኙ የጥቅም ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታዎች አሉ፡፡

የጥቅም ግጭትን በአይነት ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም በብዛት የሚከሰቱ የጥቅም ግጭቶች አራት ናቸዉ፡፡ የገንዘብ ፍለጋ፣ የውጭ ስራ፣ የቀረቤታ ስራ እና የስጦታ የጥቅም ግጭት ናቸው፡፡

የገንዘብ ፍለጋ ጥቅም ግጭት፡- አንድ የመንግስት ሰራተኛ ወይም ኃላፊ በተሰጠዉ ኃላፊነት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለግል የገንዘብ ማግኛ አድርጎ ሲገለገልበት ነዉ፡፡

በአንድ በኩል ከተሰጠዉ የሥራ ኃላፊነት ውጭ የሚሰራ የውጭ ሥራ ጥቅም ግጭት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ በመንግስት የስራ ሰዓት ከተሰጠዉ የሥራ ኃላፊነት ውጪ በግሉ ሲሰራ ሲገኝ የጥቅም ግጭት ተፈጠረ የሚያስብል ነው፡፡

በሌላ በኩል የጥቅም ግጭት በመቀራረብና በመግባባት ይፈጠራል፡፡ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በመንግስት መስሪያቤት ውስጥ ሲሰራ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመቀራረብ፣ በዝምድና ትውዉቅ በመመስረት አገልግሎት ሲሰጥ ቢገኝ በቀጥታ የጥቅም ግጭት ይከሰታል፡፡

ስጦታ ወይም ግብዣ መቀበል ወይም መስጠት አንዱ የጥቅም ግጭት መንስኤ ነው፡፡ የመንግስትን የአሰራር ሂደት ሊያደናቅፍ የሚችል ስጦታ መስጠት እና መቀበልን የጥቅም ግጭት ዉስጥ ያስገባል፡፡ ይህ ሁኔታ ባለጉዳዩ በሂደት ለሚፈልገዉ ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ላልሆነ አገልግሎት ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል የጥቅም ግጭት ይፈጥራል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጸሙ የሰራተኞች ወይም የኃላፊዎች የጥቅም ተግባራት የድርጅቱን ወይም መስረያ ቤቱን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የጥቅም ግጭትን ከግል ማህበራት አንጻር መመልከት ይቻላል፡፡ ማህበራት በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊዉን መስፈርት ሲያሟሉ (አዋጅ ቁጥር 985/2009) ይቋቋማሉ፡፡ ማህበራት የሚተዳደሩበት የራሳቸዉ መተዳደሪያ ህግ /memorandum of association/ አላቸዉ፡፡ የማህበራት ዝርዝር የስራ አፈጻጸሞች በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ተመላክቷል፡፡

ስለሆነም በአንቀጽ 217 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት ሌሎች የማህበሩ ሸሪኮች ካልፈቀዱ በስተቀር ማንኛውም ኃላፊነቱ ያልተወሰነ ሸሪክ ማህበሩ የሚሠራቸውን ተመሳሳይ ሥራዎች ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገን ለማከናወን እንዲሁም በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ በሚያደርግ ተመሳሳይ ዓላማ ባለው ሌላ ማህበር ውስጥ አባል መሆን አይችልም ሲል ይደነግጋል፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት አባል በሆነበት ድርጅት ጋር የጥቅም መጋጨት እንዳይፈጠር ለመከላከል ዓላማ ነው፡፡

በአጠቃላይ ማንኛውም ሰራተኛ ከተጣለበት ኃላፊነት ውጭ ለግሉ፣ ለቤተሰቡና ለወዳጁ እንዲሁም ለማናቸውም ዓላማ ሲባል ከተቋሙ ጥቅም የሚጋጭ ተግባር መፈጸም የተከለከለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የጥቅም ግጭት ተቋሙን ከመጉዳት አልፎ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ወይም ብልጽግና አስገኝቶ ከሆነ አግባብ ባለዉ ህግ የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡

ስለሆነም በየትኛዉም ደረጃ ያለ ሰራተኛ ለተቀጠረበት ተቋም ተገቢዉን አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ በተቋሙ ዉስጥ እያገለገለ/ች ከስራው/ዋ ጋር በተገናኘ ለሚፈጠር ጥቅም ራሱን በማግለል ታዓማኒነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

You May Also Like

More From Author

+ There are no comments

Add yours