ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ግዢ ጋር ተያይዞ የተከሰሱ 8 ግለሰቦችና 1 ድርጅት ጥፋተኛ ተባሉ

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 7/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ግዢ ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ስምንት ግለሰቦች እና አንድ ድርጅት በሌሉበት ጥፋተኛ ተባሉ።

ሌሎቹ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንትር ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች በ1ኛ ክስ እንዲሁም 2ኛ እና 3ኛ ክስ በአንድ ክስ ተጠቃሎ እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብይን ሰጠ።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) የቀረበባቸው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ በማቅረብ ምንጩን ደብቀዋል ወይም አሽሽተዋል በሚል የቀረበባቸውን 4ኛ ክስን በሚመለከት ወደ ባለቤታቸው ሂሳብ ገንዘብ ማስገባታቸው አሽሽተዋል ለማለት አያስችልም በሚል ነጻ ተብለዋል።

ሆኖም ግን ገንዘብ ገቢ ሆኖላቸዋል የተባሉት የ1ኛ ባለቤት የሆኑት 15ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ፀሃይ ሀይሉ ግን ወደ ሂሳባቸው የገባውን ገንዘብ ለማሸሽ ቤት በመግዛት ለግል ጥቅም አውለውታል በሚል በቀረበባቸው ማስረጃ መሰረት በሌሉበት ጥፋተኛ ተብለዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ከነበሩ ሁለት የኮንስትራክሽ የግል ድርጅቶችንና 16 ግለሰቦች መካከል ያለመከሰስ መብታቸው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተነሳው የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ፣ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ (ዶ/ር)፣ የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ም/ፕሬዚዳንት አብርሐም ባያብል (ኢ/ር)፣ የግዢ ዳይሬክተር የነበሩት ሊበይ ገልገሎ፣ የግዢ ዳይሬክተር የሆኑት ቦሩ ህርቦዬ፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው መምህርና የቢኤች ዩ አማካሪ ለታ ድሪባ ጨምሮ ጠቅላላ ስራ ተቋራጮችና የቢዳሩ ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጆችም ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ፤ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግስት ግዢ መመሪያን በመተላለፍ በሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሎች ተከሳሾችና ከስራ ተቋራጭ ጋር ያለአግባብ ግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን 52 ሺህ 812 ብር ከ81 ሳንቲም ጉዳት አድርሰዋል የሚል እና የ14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ግዢ መፈጸም እና በዚህ ማሽነሪና ተሽከርካሪ ግዢ ደግሞ 12ኛ፣ 13ኛ፣ 14ኛ፣ 16ኛ ተከሳሾች ጥቅም አግኝተውበታል በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን የተከሳሽ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ሰፋ ያለ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው ዝርዝር ክስ በችሎት ለቀረቡ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር ለተጠቀሱ ተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገና በችሎት ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾቹም በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ፍሬ ነገሩ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ሕግም የክሱን ግልጽነት በመጥቀስ ክሱ ሊሻሻል አይገባም በማለት የሰጠውን የጽሁፍ መልስ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው የተከሳሾች ጥያቄ አግባብነት ያለው አይደለም በማለት የክስ መቃወሚያ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ብይን ሰጥቷል።

ከብይኑ በኋላ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት ከሚረሚያ ቤት ቀርበው በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህም በኋላ ዐቃቤ ሕግ ከ10 በላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ያቀረበ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የምስክር ቃል መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በ1ኛ ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እንዲከላከሉ የተባሉ ሲሆን በዚሁ ክስ የተካተተው 8ኛ ተከሳሽ በሌለበት ጥፋተኛ ተብሏል።

በሌላ በኩል ችሎቱ የተሽከርካሪ ግዢን የሚመለከተው 3ኛው ክስ የግንባታ ግዢ ላይ ከሚያተኩረው ከ2ኛ ክስ ጋር እንዲጠቃለል በማለት በዚህ ክስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

በዚሁ በተጠቃለለው ክስ የተካተቱ በሌሉበት ጉዳያቸው የታዩት ከ8ኛ እስከ 13 ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እንዲሁም 16ኛ እና 18ኛ ተከሳሽ በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።

የተሽከርካሪና የማሽነሪ ግዢን በሚመለከተው ክስ ላይ ተካተው የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ አይመን አብዱላሂና እና 17 ተከሳሽ አረብ ኮንስትራክሽን የግል ድርጅት በሚመለከት በቂ ማስረጃ ያልተሰማባቸው መሆኑ ተጠቅሶ ነጻ መባላቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በ4ኛ ክስ ከባለቤታቸው ጋር የተከሰሱት 1ኛ ተከሳሽ ጫላ ዋታ ዶ/ር የቀረበባቸው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ ተብሎ የተመሰረተባቸው ክስ ወደ ባለቤታቸው ሂሳብ ገንዘብ ማስገባታቸው ብቻ አሽሽተዋል ለማለት አያስችልም በማለት ነጻ ተብለዋል።

ሆኖም ግን ገንዘብ ገቢ ሆኖላቸዋል የተባሉት የ1ኛ ተከሳሽ ባለቤት የሆኑት 15ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ፀሃይ ሀይሉ ግን ወደ ሂሳባቸው የገባውን ገንዘብ ምንጭ ለማሸሽ ቤት በመግዛት ለግል ጥቅም አውለውታል በሚል በቀረበባቸው ማስረጃ መሰረት በሌሉበት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ ሰባት ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ከሐምሌ 22 ጀምሮ ለአምስት ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

You May Also Like

More From Author

+ There are no comments

Add yours