በሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ከማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት ጋር ዉይይት ተካሄደ

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ከማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት ጋር በሀዋሳ ከተማ ዉይይት አካሂዷል።

የዉይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ዘላለም ለማ እንደገለፁት ፖሊሲዉ እንደ ሀገር በተቋማት ዉስጥ የሚፈፀም የሙስና ወንጀል ለመቅረፍ ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዉ፥ ፖሊሲዉ እንዲጠናከር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽነሯ አክለዉም ቀጣይነት ያለዉ ሀገራዊ እድገት ለማረጋገጥ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት እንዲሁም ለዜጎች የተመቻቸ ማህበራዊ ህይወት ለመፍጠር በሚደረገዉ ትግል ሙስና እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዉ፥ ለዚሁ ትግል ፖሊሲው መዘጋጀቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለዉ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ረዥም ጊዜ ቢሆነዉም የአሰራርና የህግ ማዕቀፍ በፖሊሲ ደረጃ እንዳልነበረ የገለፁት ኮሚሽነሯ፥ ፖሊሲዉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ትግል ለማድረግ እና የሥነምግባር ግድፈቶችን ከማረም አኳያ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በእለቱ ለውይይቱ መነሻ የሚሆን የረቂቅ ፖሊሲውን ሰነድ በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መልካሙ መንገሻ የቀረበ ሲሆን፥ በቀረበዉ የመወያያ ሰነድ መነሻነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ዉይይት ተደርጎ ግብዓት ተወስዷል።

የውይይት መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት እንደሚቀጥል ከኮሚሽኑ የፌስቡክ ገፅ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

You May Also Like

More From Author

+ There are no comments

Add yours