ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል የዜጎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከልና ለፀረ-ሙስና ትግሉ የዜጎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ከከተማው ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል ዜጎችን አሳታፊ ለማድረግ በሀገር አቀፍ የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ረቂቅ ፓሊሲ ላይ ከቢሮው ባለድርሻ አካላት ጋር ወይይት አድርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ውይይቱን በከፈቱበት ወቅት ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከልና ለፀረ-ሙስና ትግሉ የዜጎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ የውይይት መድረክ ማካሄድ ማስፈለጉን ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ አያይዘውም የሥነምግባር ብልሽት መኖር ለሀገረ መንግስት ግንባታ ፈታኝ መሆኑን ጠቁመው፣ እንደ ኮሚሽን ሥነምግባር ያለው ትውልድ ለማፍራት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ጎን ለጎን በብልሹ አሰራር ውስጥ ገብተው የተገኙ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰዱ በማድረግ የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ታደሰ በበኩላቸው ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የቀረበው ረቂቅ ፓሊሲ ላይ ባለድርሻ አካላት ለሰጡት ሀሳብና አስተያየት ምስጋና አቅርበው፣ የትውልድ ሥነምግባር ግንባታ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የፓሊሲው ዋና ዋና ጉዳዮች በሰባት መሠረታዊ ነጥቦች የተቀመጡ ሲሆን፣ የሥነምግባር መርሆዎች፣ የህፃናትን ሥነምግባር በማነፅ የቤተሰብ ሚና፣ የወጣቶች ሥነምግባር፣ የተቋማት የሥነምግባር ግንባታ ስራዎች፣ የተቋማት የውስጥ መከላከል አሰራር ስርዓት፣ የሙስና ወንጀል ህግ አተገባበር እንዲሁም የተመዘበረ ሀብት የማስመለስና ማስተዳደር በሚሉ ሀሳቦች ላይ ውይይቱ አተኩሯል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የተለያዩ ዘርፎች ፓሊሲው በደንብ ቢያያቸው፣ የሚባክኑ የመንግስት ሀብቶችን የሚቆጣጠርበት ጥብቅ መመሪያ ቢዘጋጅ፣ ረቂቅ ፖሊሲው ላይ ህዝቡ በስፋት ውይይት ቢያደርግ የሚሉና ሌሎችም አስተያየቶች ቀርበው በመድረኩ ላይ ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

You May Also Like

More From Author

+ There are no comments

Add yours