6133 0115533852 / 0935947533Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለውዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ ተሰረዘ፡፡

በኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ግዥ ጠያቂነት የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ2014 በጀት ዓመት የወባ መከላከያ አጎበር ግዥ ለመፈጸም ኖቬምበር 10-2021 በወጣው የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ በጨረታ ቁጥር Tender No:ICB/EPSA6/MOH-GF/LLINS/MS/23/ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ከወጣው የግዥ ጨረታ ጋር በተያያዘ የግዥ ሂደቱ “ህግን የተከተለ አይደለም ” የሚል ጥቆማ ለፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ ከየካቲት 8-24/2014 ዓ.ም በአስቸኳይ የሙስና መከላከል የማጣራት ሥራ አከናውኗል፡፡የቀረበውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ በአደረገው የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ አሸናፊ ተደርጎ የተመረጠው ድርጅት የአገር ውስጥ የወባ መከላከያ አጎበር የማረጋገጫ ፍቃድ (የምስክር ወረቀት) የሚሰጡና የሚያድሱ አካላት ኃላፊነት በግልፅ አለመቀመጡን እንደ ምክንያት አድርጎ በመውሰድ ካስቀመጣቸው ሶስት ወኪሎች በአንደኛው ተወካይ ህግን ባልተከተለ መልኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ህገ-ወጥ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የወሰደና በጨረታው እንዳይወዳደር የተሰረዘበት ሲሆን በሌላኛው ተወካይ በተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት በመወዳደር የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን መደረጉ፣የዋናውን ድርጅት (Principal Agent) ከተጠያቅነት እንደማያድነውና የግዥው ሂደት ጤናማ አለመሆኑ ከማጣራት ሂደቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ባረጋገጠቸው ግኝቶች ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ግዥውን ከሚፈፅመው ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ተይዟል፡፡ ይህ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ ለ17,809,388 የወባ መከላከያ አጎበሮች ግዢ ጨረታ የወጣ ሲሆን ሂደቱ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በማጣራት ግኝቱ የማስተካከያ ምክረ-ሀሳቦችን የያዘ ሪፖርት ለጤና ሚኒስቴር እና ከላይ ለተመለከቱት መንግሥታዊ ተቋማት አሳውቋል፡፡ከዚህ በመነሳት የኤፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በቀን 09/09/2014 ዓ/ም፤ በቁጥር መጠ1/17/40/723 በፃፈው ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እያሉ የዓለም አቀፍ ጨረታ ሂደቱን ባለበት ሁኔታ ማስቀጠል በግዢዉ ሂደት ላይ የነበረን ስጋት እንዲቀጥል የሚያደርግና ውጤቱ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አሉታዊ ተፅኖ ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን ሰርዟል፡፡ይህንኑ ውሳኔ ተጫራቾች እንዲያውቁት እንዲደረግ ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አሳወቋል፡፡ ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረ-ሀሳብ ተቋማት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በራስ ውሳኔ ወደ መከላከል የሚያደርስ በመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህንኑ ምክረ ኃሳብ በመቀበል የእርምት እርምጃ መውሰዱ አርያነት ያለው ተግባር ነው፡፡በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጨረታው ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመተጋል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ስለሆነ ኮሚሽኑ ያለውን ከፍተኛ አድናቆትና እውቅና የሰጠ ሲሆን ሌሎች የመንግሥት መ/ቤቶች፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ህዝባዊ ድርጅቶች ይህንን አርአያነት ያለውን ተግባር በመውሰድ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያለውን እምነት ለመግለፅ ይወዳል፡፡

ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያ!

Related Posts

Leave a Reply