6133 0115533852 / 0935947533Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ላይ ያካሄደውን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ጥናት ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 15/ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ)፡- የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ላይ ያካሄደውን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ጥናት ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡ ኮሚሽኑ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ጥናቱን ያካሄደው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በ2014 በጀት ዓመት 17, 809, 388 (አስራ ሰባት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ ስምንት) የወባ መከላከያ አጎበር ግዥ ለመፈፀም በጨረታ ቁጥር Tender No: ICB/EPSA6/MOH-GF/LLINS/MS/23/21 አውጥቶት የነበረው የግዥ ጨረታ ህግን ተከትሎ የተፈፀመ አይደለም በሚል በቀረበ ጥቆማ መነሻነት ነው፡፡ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ጥናቱ የተከናወነው በተቋማት በአካል በመገኘት ለጥናቱ የሚያስፈልጉ ሰነዶችና መረጃዎችን በማሰባሰብ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ነው፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው በጨረታው ለመሳተፍ የጨረታ ሰነድ ከገዙት 27 ተጫራቾች ውስጥ 8ቱ የጨረታ ሰነዱን ሞልተው ያስገቡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በጨረታ ሂደቱ አሸናፊ ተደርጎ የተመረጠው “Fujian Yamei Industry and Trade Co. Ltd.” የተባለው ድርጅት “DROGA, MAJIOR and ATMA” የተባሉ ሦስት ወኪሎች አሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ “DROGA” ለተባለው ወኪሉ የተሰጠው የምዝገባ ሰርተፊኬት ጋር በተያያዘ የኋላ ፋይሉ ሲታይ ህጋዊ አሠራርን ባልተከተለ መንገድ በተጭበረበረ መንገድ የወጣና በዚህ መሰረት ድርጅቱ እንደ ዋና ተጫራች ተደርጎ የተወሰደ መሆኑ ሲታይ የግዥ ሂደቱ የአሰራር ክፍተት የነበረበት መሆኑ፣”DROGA” የተባለው ወኪል የማጭበርበር ድርጊቱ ታውቆ በኢትዮጵያ መድኃኒትና ምግብ ባለስልጣን ከተሰረዘ በኋላ አሸናፊው ድርጅት “ATMA” በተባለው ሌላው ወኪሉ ጨረታውን እንዲሳተፍ መደረጉ የነፃ ገበያ ሂደትን የሚጎዳ መሆኑ፣ግዥ እንዲፈፀምለት የጠየቀው የጤና ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባ ከግብርና ሚኒስቴርና የዓለም የጤና ድርጅትን የብቃት ደረጃ ያሟላ ሆኖ እንዲወሰድለት ቢጠይቅም ከዚህ በተጨማሪ እንዲወሰድ መደረጉና የግብርና የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባ እንደአማራጭ መታየቱ፣ ከፍቃድ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በግብርና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን መካከል የሀላፊነት ግልፅነት መጓደል መኖሩ በጥናት ግኝቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ ከጥናቱ ግኝቱ በመነሳት ኮሚሽኑ የሚከተሉትን የውሳኔ ምክረ-ሀሳቦችን አቅርቧል፡-•በጨረታው አሸናፊ የተባለው ድርጅት ሶስት ወኪሎች አድርጎ በአንደኛ የተጭበረበረ የብቃት ሰርተፊኬት ማውጣቱ ሲታወቅ በጨረታው እንዳይወዳደር መደረግ የነበረበት መሆኑን፣ •አሸናፊ የተባለው ድርጅት “Droga” በተባለው የሀገር ውስጥ ወኪሉ አማካኝነት የተጭበረበረ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አውጥቶ የነበረ በመሆኑ በተመሳሳይ የግዥ ሂደቶች እንዳይሳተፍ ቢደረግ፤•ጉዳዩ የሚመለከተው የኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን የወባ አጎበር ለማቅረብ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አወሳሰድ ጋር ለተፈፀመው የማጭበርበር ድርጊት የበኩሉን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ቢደረግ፣ •አንድ ተጫራች ከአንድ በላይ የሆነ ወኪል ይዞ በአንድ ጨረታ ለመሳተፍ ሲሞክር የነፃ የወድድር ሂደት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድርና ለብልሹ አሰራር ክፍተት ሊፈጥር የሚችል መሆኑን፣•ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ግልፅ የሆነ አሰራር እንዲዘረጉና በታዩ የአሰራር ክፍተቶች ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ቢደረግ፣•በግዢ ሂደቱ ውስጥ የነበሩና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በተጠቀሰው የግዥ ሂደት የታየውን የአሰራር ችግር እንዲፈቱ፣ኮሚሽኑ ያካሄደውን አስቸኳይ የሙስና ጥናት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር፣ ለኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር፣ ለኢፌዲሪ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሚኒስትሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ባካሄደው የመውጫ ውይይት ስለጥናቱ ሂደትና ስለተገኙ ውጤቶች ግልፅነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባደረገው የአስቸኳይ ጥናት መሰረት የወባ መከላከያ አጎበር ግዥው እና የብቃት ሰርተፊኬት አሰጣጥ ሂደቱ ግልፅነት የጎደለው እንደነበር ማየት የተቻለ ሲሆን የሂደቱን ጥራት የሚያጓድል ሆኖ በመገኘቱ በተሻሻለው የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ለማሻሻለው በወጣው አዋጅ ቁጥር 1236/2013 አንቀፅ 7 ንዑስ አንቀፅ 4 መሰረት ማሰተካከያ እንዲደረግ ምክረ-ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን በጉዳዩ ላይም የቅርብ ክትትል እንደሚያደርግ ገልፆል፡፡ኮሚሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር በሚቀርቡለት ጥቆማዎች መነሻ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ጥናት ሪፖርትን በዚህ ሁኔታ ይፋ ማድረግ መደበኛ አሰራሩ መሆኑን እያስገነዘበ የተቋማት አመራሮች ለጥናቱ ሂደት ቀና ትብብር ስላደረጉ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

Related Posts

Leave a Reply